Blog

የኬሚካሎች ብክለት ሥጋት እየጨመረ ነው

ከአገር ኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ተያይዞ የኬሚካሎች ዝውውርና ክምችት እየተስፋፋ በመሄዱ፣ የተለያዩ ኬሚካሎች ብክለት ሥጋት እየጨመረ እንደመጣ ተገለጸ፡፡
ይህ የተገለጸው ማክሰኞ መስከረም 29 ቀን 2011 ዓ.ም. በጁፒተር ሆቴል በተከፈተው ዓለም አቀፍ የኬሚካል ደኅንነትና አስተዳደር ጉባዔ ላይ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ የኬሚካል መሣሪያዎች መከላከል ድርጅት ለሦስት ቀናት በአዲስ አበባ በማካሄድ ላይ ባለው ሥልጠና፣ አገሮች ጅምላ ጨራሽ ኬሚካል መሣሪያዎችንና አደገኛ ኬሚካሎችን እንዴት መቆጣጠር እንደሚችሉ ሰፊ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡ በሥልጠናው ላይ የታሰተፉ ባለሙያዎች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኬሚካል መሣሪያዎች ዝውውር በኢትዮጵያ አሳሳቢ ባይሆንም ከግብርና ቴክኖሎጂዎችና አምራች ኢንዱስትሪ መስፋፋት ጋር የአደገኛ ኬሚካሎች ብክለት ሥጋት እየጨመረ መጥቷል፡፡ አሳሳቢ የሆኑ የኬሚካል ብክለት ሥጋቶች በሁለት መንገዶች እንደተጋረጡ ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡

አንደኛ ለተለያዩ አገልግሎቶች ወደ አገር ውስጥ ገብተው የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸው ተከማችተው የሚገኙ አደገኛ ኬሚካሎች ናቸው፡፡ እነዚህ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ፀረ ተባይ፣ ፀረ አረም፣ ማዳበሪያዎችና ሌሎች የተለያዩ ኬሚካሎች ሲሆኑ፣ በአዲስ አበባና በተለያዩ የክልል ከተሞች ተከማችተው ይገኛሉ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥቅም ላይ እንዳይውል የተከለከለው ዲዲቲ ብቻ ከ1,400 ቶን በላይ በአዲስ አበባ፣ በአዳማና በሐዋሳ ከተሞች ተከማችቶ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ የአደገኛ ኬሚካሎች አስተዳደርና አወጋገድ ሥርዓት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ያልነበረ በመሆኑ፣ በማንና እንዴት እንደገቡ የሚገልጽ ሰነድ የሌላቸው በርካታ አደገኛ ኬሚካሎች በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ተከማችተው እንደሚገኙ ባለሙያዎቹ አስረድተዋል፡፡
የኬሚካሎች ምዝገባ፣ የአወጋገድ ሥርዓትና ማስወገጃ ተቋም ወይም ቦታ ባለመኖሩ እነዚህ ኬሚካሎች ለማኅበረሰብ ጤናና አካባቢ አደገኞች ናቸው ተብሏል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ የተጠቀሰው ብክለት ከተለያዩ ፋብሪካዎች በሚወጡ ዝቃጮች ነው፡፡ በተለይ ከቆዳ፣ ከቀለምና ከጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች የሚወጡ እንደ ሜርኩሪና ሊድ ያሉ ከባድ ብረቶች ወንዝ ውስጥ በመግባት፣ በሰው ልጅ ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርሱ ባለሙያዎቹ ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባና በአካባቢዋ የሚገኙ የቆዳና የቀለም ፋብሪካዎች ከውኃ ጋር ተቀላቅለው የሚወጡ አደገኛ ኬሚካሎችን ወደ ወንዞች በመላክ፣ በአካባቢና የሰው ልጆች ላይ ከፍተኛ ቀውስ በመፍጠር ላይ እንደሆኑ ይገልጻሉ፡፡ እነዚህ እንደ ሜርኩሪና ሊድ ያሉ በውኃና አፈር ውስጥ ገብተው ለረዥም ጊዜ መቆየት የሚችሉ አደገኛ ኬሚካሎች ካንሰር ሊያመጡ እንደሚችሉ፣ በተለይ በአቃቂ ወንዝ ላይ ከፍተኛ ብክለት እየተከሰተ በመሆኑ ናሙና ተወስዶ ምርምር ሊካሄድ እንደሚገባ፣ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ በሚገኙ ወንዞች ዳርቻ የሚመረቱ አትክልቶች ጉዳይ ትልቅ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡

በስብስባው ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዮሐንስ ድንቃየሁ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የአገልግሎት ጊዜ ያለፈባቸው አደገኛ ኬሚካሎች በአገር ውስጥ ሊወገዱ አይችሉም፡፡ ኬሚካሎቹ ሊወገዱ የሚችሉት ወደተመረቱበት አገር ተልከው እንደሆነ የገለጹት አቶ ዮሐንስ፣ ይህን ለማድረግ በጀት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡ በተከማቹ ኬሚካሎች ላይ የሚሠራ ግብረ ኃይል በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስተባባሪነት መቋቋሙን የገለጹት አቶ ዮሐንስ፣ ኬሚካሎቹ የት እንደሚገኙና ዓይነታቸውና መጠናቸውን ለይቶ ኬሚካሎቹን ለማስወገድ የሚያስፈልገው የበጀት መጠን አጥንቶ ለማቅረብ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ከግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴርና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ በመሥራት ላይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ሃላላ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በኬሚካል ምርት አጠቃቀምና ዝውውር ላይ ቁጥጥር ለማካሄድ የሚያስችል የኢንዱስትሪ ኬሚካል ምዝገባና አስተዳደር አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ ወጥቷል፡፡ በአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር የተረቀቀው አዋጅ ከውጭ የሚገቡና በአገር ውስጥ የሚመረቱ ኬሚካሎች በማዕከልነት መመዝገብና መቆጣጠር የሚያስችል እንደሆነ የገለጹት አቶ ሳሙኤል፣ በቀጣይ ደንቦችና መመርያዎች ወጥተውለት ሥራ ላይ እንደሚውል ተናግረዋል፡፡
‹‹ኬሚካሎችን የመከታተልና መቆጣጠር ኃላፊነት ለኢንስቲትዩቱ የተሰጠ በመሆኑ ከአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በዝርዝር ጉዳዮች ላይ ለመሥራት በዝግጅት ላይ ነን፤›› ብለዋል፡፡ ይህ ትልቅ ኃላፊነት የተጣለበት የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት፣ የኬሚካል ምርመራዎች የሚያካሂድበት አንድም ቤተ ሙከራ እንደሌለው ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ከተመሠረተ አራት ዓመታት የሆነውና ትልቅ አገራዊ ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም ቤተ ሙከራ የሌለው በመሆኑ ሥራውን በብቃት ለመወጣት እንደሚቸገር ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡
አቶ ሳሙኤል ለትችቱ በሰጡት ምላሽ ኢንስቲትዩቱ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ቤተ ሙከራዎችን እንደሚጠቀም ገልጸው፣ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በተሰጠ መመርያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚሰጣቸው ቦታ የዋና መሥሪያ ቤትና የቤተ ሙከራ ሕንፃ መገንባት እንደሚጀምር ገልጸዋል፡፡ በአገሪቱ ተከስቶ በነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት የአዲስ አበባ አስተዳደር የግንባታ ቦታ ለማዘጋጀት ተስኖት እንደነበር ገልጸው፣ ይህ ችግር አሁን በመቀረፉ ቦታው ተዘጋጅቶ ወደ ግንባታ እንደሚገባ ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል፡፡
‹‹የኢንስቲትዩቱን አቅም እንገነባለን፡፡ የራሳችን ቤተ ሙከራም ይኖረናል፡፡ እስካሁን ግን የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችን ቤተ ሙከራዎች ስለምንጠቀም፣ የቤተ ሙከራ አለመኖር ሥራችንን ከመሥራት አያግደንም፤›› ብለዋል፡፡
ሪፖርተር

Copyright@2018 Addis Ababa City Resilience Project Office | All Rights Reserved