የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን በየቀኑ በሚያመርተው ውኃና በፍላጎት መካከል ከፍተኛ ልዩነት በመፈጠሩ፣ በይፋ ወደ ፈረቃ አሠራር መግባቱን አስታወቀ፡፡
ባለሥልጣኑ በአሁኑ ወቅት ከገጸ ምድርና ከከርሰ ምድር በቀን የማምረት አቅሙ 525 ሺሕ ሜትር ኩብ ውኃ ነው፡፡ ነገር ግን ከተማው የሚፈልገው የውኃ መጠን በቀን ከ930 ሺሕ እስከ አንድ ሚሊዮን ሜትር ኩብ ውኃ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በአቅርቦትና በፍላጎት መካከል ካለው ከፍተኛ ልዩነት በተጨማሪ፣ የተመረተው ውኃ ሙሉ በሙሉ ለነዋሪዎች እንዳይደርስ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና የቴክኒክ ብልሽቶች ምክንያት መሆናቸው ታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘሪሁን አባተ (ኢንጂነር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በተፈጠረው ችግር ምክንያት ቢያንስ በ12 እና በ24 ሰዓት ልዩነት ውኃ ያገኙ የነበሩ አካባቢዎች፣ አሁን እስከ አሥራ ሶስት ቀናት ድረስ ይዘገይባቸዋል፡፡
‹‹በአዲስ አበባ በተለያዩ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጦች ላይ የሚገኙ አካባቢዎች ስላሉና ነዋሪዎችም በምድርና በሕንፃ ውስጥ የሚኖሩ ስለሆኑ፣ ቢያንስ በሳምንት ሦስት ጊዜ ውኃ ለማዳረስ ይሠራል፤›› ሲሉ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፣ የክረምት ወራት በቅርቡ የወጣ እንደመሆኑ ግድቦች መያዝ ያለባቸውን የውኃ መጠን ይዘዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን ከተማው እየሰፋ በመሄዱ ውኃ በብዛት የሚፈልጉ ኢንዱስትሪዎች እየተስፋፉ ስለሆነ፣ የውኃ ፍላጎት እየጨመረ ነው፤›› ብለዋል፡፡
‹‹የአጭር ጊዜ ዕቅድ በፈረቃ ማድረስ ቢሆንም፣ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ስለሆነ በፍጥነት በማጠናቀቅ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እየተሠራ ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የተወሰኑ ሠራተኞች ለችግሩ መባባስ አሻጥር ይሠራሉ እየተባለ ስለሚነገረው ጉዳይ ለዋና ሥራ አስኪያጅ ጥያቄ ቀርቦላቸው ሲመልሱ የባለሥልጣኑ ሠራተኞች መልካም መሆናቸውን፣ የተወሰኑ ሠራተኞች ግን በዚህ ዓይነት ድርጊት የተሠማሩ ስለመሆኑ ሲነገር እንደሚሰማ፣ ዕርምጃ መውሰድ የሚያስችል ማስረጃ ግን እንደሌለ አስረድተዋል፡፡
ሪፖርተር
በምርትና በፍላጎት መካከል ከፍተኛ ክፍተት በመፍጠሩ ውኃ በፈረቃ ማዳረስ ተጀመረ