Blog

የወንዞች እና የወንዝ ዳርቻ አረንጓዴ መናፈሻ ፕሮጀክት በይፋ ስራ የማስጀመር ስነ-ስርዓት ኢ/ር ታከለ ኡማ፣ በተገኙበት ተከናውኗል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ አነሳሽነት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “የወንዞች እና የወንዝ ዳርቻ አረንጓዴ መናፈሻ” ፕሮጀክት በይፋ ስራ የማስጀመር ስነ-ስርዓት ኢ/ር ታከለ_ኡማ፣ የፌደራልና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች በተገኙበት ተከናውኗል፡፡
የወንዝ ዳርቻ የልማት ፕሮጀክቱ የሚያተኩረው በአዲስ አበባ አቋርጠው በሚያልፉ ሁለት ታላላቅ ወንዞች ላይ ነው፡፡

 

እነዚህ ከእንጦጦ ተራራ እስከ አቃቂ ወንዝ የሚዘረጉ ወንዞች ህዝብ በብዛት የሚኖርባቸው የከተማዋ አከባቢዎችን አቋርጠው የሚያልፉ ሲሆን በቅደም ተከተል 23.8 ኪ.ሜ እና በ27.5 ኪ.ሜ ይረዝማሉ፡፡

ይህ ፕሮጀክት ሶስት ዋና ዋና ዓላማዎች አሉት ፦

1. ታሪካዊ ወንዞችን እና የወንዝ ዳርቻዎችን መልሶ በማልማት አዲስ አበባን የከተማ ቱሪዝም መዳረሻ ማድረግ

2. የጎርፍ መጥለቅለቅን በመቀነስና የህዝብ መናፈሻ ቦታዎችን ፣ የብስክሌት መንገዶችን እና የወንዝ ዳርቻ የእግር መንገዶችን በመፍጠር የከተማዋን ነዋሪዎች ደህንነት ማረጋገጥ፤

3. የአረንጓዴ ቦታዎች እና ተያያዥ አገልግሎት ዘርፎችን በማጠናከር የአገሪቷን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ የመገንባት ህልም እውን ማድረግ ናቸው፡፡

 

የአዲስ አበባ የተፋሰስ ወንዞች ዳርቻ ፕሮጀክት ለአዲስ አበባ አረንጓዴ ልማት ፣ የተፈጥሮ ሃብቷን ለማሳደግ እና ለማስፋፋት የሚያስችል አስተዋፅዖ እንደሚኖረው ይታመናል፡፡

ፕሮጀክቱ የከተማዋ ነዋሪዎች ደህንነት በማሻሻልና የከተማዋን እይታ ይበልጥ በመለወጥ ረገድ ብዙ ሚና ከመጫወቱ በተጨማሪ፦

• የተለያዩ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መስህቦች እንዲሁም ለጎብኚዎች የእረፍት ጊዜ ማሳለፊያ ስፍራዎችን በማዘጋጀት የውጪ አገርና የአገር ውስጥ ጎብኚዎች ወደ አዲስ አበባ መሳብ፤

• በፕሮጀክቱ ወቅት ለከተማዋ ነዋሪ ተጨማሪ የስራ ዕድል መፍጠር፤

• በወንዞች ዳርቻ እና ህዝብ በሚንቀሳቀስባቸው ቦታዎች የአገልግሎት ዘርፉን በማበረታታት ካፌዎች ፣ ምግብ ቤቶች ፣ የከተማ አስጎብኚዎችና የመሳሰሉ አገልግሎቶችን ማመቻቸት፤

• የተፋሰስ ወንዞች ዳርቻ እና ፕሮጀክቱ ዳርቻ ያሉና ወደፊት የሚገነቡ የሪልስቴት ፕሮጀክቶችን የንብረት ባለቤትነት እድገት መጨመር፤

• የአረንጓዴ ሽፋንን በማሳደግ የአዲስ አበባን ገፅታ በመገንባት ከተማዋን እንደስሟ አዲስ አበባ ለማድረግ ያለመ ፕሮጀክት ሲሆን የቤተ-መንግስት አከባቢ የከተማ መናፈሻ የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ክፍል መሆኑ ይታወቃል፡፡
፨ በ3 ዓመታት ውስጥ የሚጠናቀቀው፣ 56 ኪ.ሜ የሚሸፍነው እና 29 ቢሊዮን ብር ውጪ ይደረግበታል ተብሎ የሚገመተው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት፦

•በ29 ቢሊዮን ብር ወጭ ይከናወናል፤ በሦስት ዓመታት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡

•ከእንጦጦ ተራራ በጉለሌ በኩል አፍሪካ ህብረት እንዲሁም ከእንጦጦ በአፍንጮ በር በባንቢስ አድርጎ አቃቂ የውሃ ማጣሪያን ይሸፍናል(56 ኪሎ ሜትር)

•ድልድዮች፣ ሰው ሰራሽ ሐይቆች፣ አረንጓዴ ቦታዎች፣ የመዝናኛ ማዕከላት፣ የውኃ ትራንስፖርት እና የንግድ ማዕከላት ይገነቡበታል።

በተያያዘ መረጃ፦ በ50 ሄክታር ላይ ተግባራዊ የሚደረግ፣ 2.5 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚደረግበት እና በ1 ዓመት ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ በተለምዶ ሸራተን ማስፋፊያ በሚባለው ቦታ ፓይለት ፕሮጀክት ይፋ ተደረጓል።

ምንጭ፦ @mayorofficeAA, ወ/ሮ መስከረም (የከንቲባው ቴክኒካል አማካሪ) ለTIKVAH-ETH,

Copyright@2018 Addis Ababa City Resilience Project Office | All Rights Reserved