Blog

አዲስ አበባ የዕውቀት ማከማቻና ማስተዳደሪያ ሥርዓት ባለቤት ልትሆን ነው

አዲስ አበባ በከተማዋ ካሉ ማነቆዎች አንዱ የሆነውን የመረጃ እጥረት ለመቅረፍ የሚያስችልና በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ውስጥ ተግባራዊ የሚሆን ‹‹የዕውቀት ማከማቻና ማስተዳደሪያ ሥርዓት›› ሊዘረጋላት ነው፡፡

በአዲስ አበባ የመጀመርያ የሆነው የዕውቀት ማከማቻና ማስተዳደሪያ ሥርዓት ፕሮጀክትን አስመልክቶ፣ ሐሙስ ታኅሣሥ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. በጌትፋም ሆቴል በተካሄደ ውይይት ላይ እንደተገለጸው፣ ፕሮጀክቱን ያዘጋጁት የአዲስ አበባ ከተማ ሬዚሊየንስ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት፣ የአዲስ አበባ የኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኤጀንሲና የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት በትብብር ነው፡፡

ፕሮጀክቱ በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ሥርዓቱም የከተማውን ዕውቀት፣ ልምድ፣ ጥናት፣ ምርምር፣ ታሪክና መረጃ ሰንዶ በዘመናዊ ሥርዓት በማስቀመጥ ለመረጃ ፈላጊዎች ባሉበት ሆነው መረጃ እንዲያገኙ ያስችላል፡፡

ከተማዋን የዘመናዊ ዕውቀት ማከማቻና ማደራጃ ባለቤት ያደርጋታል የተባለው ይህ ፕሮጀክት፣ በከተማው ያሉ ቢሮዎች ከተጠቃሚው፣ ተጠቃሚውም ከቢሮዎች በቀላሉ መረጃ እንዲያገኙ ያግዛል ተብሏል፡፡

ፕሮጀክቱ የየመሥሪያ ቤቱ አመራሮች ውሳኔ በመስጠት ላይ ያለባቸውን ችግር ለመፍታት ከማስቻሉም ባሻገር፣ የሥራ ድግግሞሽ እንዳይኖር፣ እያንዳንዱ መሥሪያ ቤት ስለሚሠራው መረጃ በመስጠት የገንዘብና የጊዜ ብክነትን ይታደጋልም ተብሏል፡፡

‹‹አዲስ ዲጂታል ቋት›› በሚል በስድስት ወር ውስጥ ሥራ የሚጀምረውን ፕሮጀክት አገልግሎት ለማግኘት ድረ ገጽ የሚኖር ሲሆን፣ ይህንንም ኅብረተሰቡ እንዲያውቀው እንደሚደረግ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ኮሙዩኒኬሽንና አውትሪች ስፔሻሊስት አቶ ዳንኤል ሽታዬ ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱም ሙሉ ለሙሉ የሚከናወነው በኢትዮጵያውያን አቅም መሆኑን አክለዋል፡፡

በኅዳር 2009 ዓ.ም. የተቋቋመው ጽሕፈት ቤቱ፣ አዲስ አበባ ያለባትን ችግር በመቅረፍ ኅብረተሰቡ ደረጃውን የጠበቀ ኑሮ እንዲኖርና ከተማዋም አደጋ የመቋቋም አቅም እንዲኖራት አልሞ እየሠራ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ሪፖርተር

Copyright@2018 Addis Ababa City Resilience Project Office | All Rights Reserved