በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገነቡ የመንገድ ላይ ፍጥነት መገደቢያዎች/ ስፒድ ብሬከሮች/ ደረጃቸውን የጠበቁ ባለመሆናቸው በተሽከርካሪ እና በመንገዶች ላይ ጉዳት በማድረስ ላይ መሆናቸውን ተገልጋዮች ሲያማርሩ ይሰማል፡፡
ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የፍጥነት መገደቢያዎች በተለያዩ አካላት የሚገነቡ መሆናቸው ወጥነት እንዳይኖር ማድረጉን በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የቤዝመትና ድልድይ ዳይሬክተሩ አቶ ኑርዬ ሙሐመድ ለኢቢሲ ገልፀዋል፡፡
በተለይም በተለያዩ የከተማ አስተዳደሮች የሚሰሩ ወጥነት የሌላቸው የፍጥነት መገደቢያዎች የተለያየ ዲዛይን ስላላቸው የቅሬታ ምንጭ ሆነው መቆየታቸውንም ኃላፊው ገልፀዋል፡፡
ችግሩን ለመቅረፍም ደረጃውን የጠበቀ የመንገድ ላይ የፍጥነት መገደቢያ ዲዛይን ተዘጋጅቶ መጠናቀቁን አቶ ኑርዬ አስረድተዋል፡፡
ከዚሁ ጋር ከአዲስ አበባ-ደሴ መስመር ላይ ካለ አግባብ የተሰሩ የፍጥነት መገደቢያዎች እንዲነሱ መደረጉን ባለስልጣኑ አመልክቷል፡፡በምትኩ በተጠና እና በአገር አቀፍ ደረጃም ወጥነት ባለው መልኩ እንዲገነባ ጥናት እየተደረገ መሆኑን የባለስልጣኑ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ተናግረዋል፡፡
ያለአግባብ የሚሰሩ የመንገድ ላይ ፍጥነት መገደቢያዎች መኪኖች በዘገምተኛ ፍጥነት እንዲጓዙ በማድረግ ከጥቅማቸው ባሻገር በርካታ አሉታዊ ጉዳቶች እያመጣ መሆኑን በርካቶች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡የትራፊክ መጨናነቅ ፣ ያልተጠበቀ አደጋ ፣የአየር ብክለት፣የጊዜና የወጭ መናር እንዲሁም እንደአምቡላንስ እና የእሳት አደጋ ላሉ መኪኖች በችግርነት ከሚጠቀሱት ጉዳዮች ውስጥ ይካተታሉ፡፡
አስተያየታቸውን ለኢቢሲ የሰጡ አሽከርከራዎች እንደሚሉት ደግሞ የፍጥነት መገደቢያዎቹ ችግር ቀራፊ እንጂ ችግር ፈጣሪ መሆን የለባቸውም ብለዋል፡፡
ኢቢሲ
በመንገዶች ላይ የሚገነቡ የፍጥነት መገደቢያዎች ወጥነት እንዲኖራቸው የሚያስችል አሰራር ሊዘረጋ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ፡፡