Blog

በአዲስ አበባ ወንዞችና በዙሪያቸው 33 የተለዩ ቦታዎች መልሰዉ እንዲያገግሙ የሚያስችል ስራ ተጀምሯል

በአዲስ አበባ ወንዞችና በዙሪያቸው 33 የተለዩ ቦታዎች መልሰዉ እንዲያገግሙ ለማድረግ  የሚያስችሉ ስራዎች መጀመሩን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወንዞችና የወንዞች ዙሪያ ልማት ፕሮጀክት ጽ/ቤት እንዳስታወቀው የከተማ ወንዞችና ምንጮች ተፋጥሯዊ ይዘታቸዉን ጠብቀዉ በሚፈሱበት ወቅት ለህብረተሰቡ ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን ይሰጡ የነበረ ቢሆንም ከግዜ በኃላ በደረሰባቸዉ ሰዉ ሰራሽ ብክለት ለህብረተሰቡ የጤና እክል እየሆኑ ነው ብሏል፡፡

የጽ/ቤቱ አስተባባሪ ዋለልኝ ደሳለኝ ለኢቢሲ እንደተናገሩት በወንዞቹ ዙሪያ የሰፈሩ 150 ሺህ ዜጎችደግሞ  ችግሩን እንዲባባስ አድርጎታል፡፡ከህብረተሰቡ የሚለቀቀው ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ  እንዲሁም  ኢንዳስትሪዎችና ፋብሪካዎች በወንዞቹ ላይ የሚለቁት የተበከለ ፍሳሽ  የወንዞቹ ህልውና አደጋ ዉስጥ እንዲወድቅ ምክንያት መሆኑን አስተባባሪው ገልፀዋል፡፡

በወንዞቹ ዙሪያ ሰፍረዉ የሚገኙ ነዋሪዎችም ፍሳሽ ከመልቀቅ ባለፈ ወንዞቹን ተጠቅመዉ በአነስተኛ መስኖ የአትክልት ልማት በማካሄድ ምርቱን  ለገበያ ማቅረባቸው በህብረተሰብ ጤና ላይ አደጋ እያስከተለ መሆኑ በጥናቶች ተመለክቷል፡፡

እናም የከተማ አስተዳደሩ እነዚህን ችግሮች ከመሰረታቸዉ እልባት ለመስጠት ያስችለኛል ያለውን ፕሮጀክት ቀርጾ ወደ ስራ መግባቱን አስታውቋል፡፡

በመጀመሪያዉ ዙር ብቻ በአዲስ አበባ ወንዞችንና የወንዞችን ዙሪያ  33 አካባቢዎች ልየታ ተካሂዶ መልሰዉ እንዲያጋግሙ ለማድረግ  የሚያስችሉ ስራዎች  እየተሰሩ መሆናቸውን የፕሮጀክት ጽ/ቤቱ  አስተባበሪ አቶ ዋለልኝ ደሳለኝ ተናግረዋል፡፡

በዚህም በሸራተን መልሶ ማልማት ዙሪያ፣ በቀጨኔ ወንዝ ላይ 6ኪሎ፣አፍንጮ በር፣ራስ መኮንን ድልድይ፣ሰራተኛ ሰፈር፣እሪ በከንቱን ይዞ የሚገኘዉን 15 ሄክታር መሬት በፓርክ ደረጃ ለማልማት ጥረት ላይ መሆኑን ጽ/ቤቱ አመልክቷል፡፡

የፕሮጀክት ጽ/ቤቱ  ስራዉን ከጀመረ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በአንዳንድ የከተማዋ ወንዞች አካባቢ የተፈጥሮ ሀብት  ስራ መሰራቱ ተስፋ ሰጪ ሆኖ መገኘቱም ተገልጿል፡፡

አሁን በመስተዳደሩ እየለሙ ያሉት በወንዞች ዙሪያ የሚገኙት መሬቶች ለመናፈሻ አገልግሎት፤ለአረጋዊያን ማረፊያና መዝናኛ እንዲሁም ለገቢ ማስገኛ አገልግሎቶች እየዋሉ መሆኑን ተመለክቷል፡፡

መስተዳድሩ የመፍትሄ ሀሳብ ያላቸዉን ይዞ ችግሮቹን በዘላቂነት እልባት ለመስጠት እንዲያስችል ከህብረተሰቡ ጋር በተቀናጀ መልኩ እየሰራ መሆኑንም ለኢቢሲ አመልክቷል፡፡

በተለይም ህብረተሰቡ የቆሻሻ አወጋጋድ ባህሉን እንዲያሻሽል አማራጮችን ማስፋትና ግንዛቤ መፍጠር፣ የወንዞችን ህልውና  አደጋ ላይ በሚጥል መልኩ የሰፈሩ ነዋሪዎችን ካሳ ከፍሎ በማንሳት  ችግሩን በዘላቂነት መፍታት እንዲሁም ኢንዱስትሪዎች ለሚለቁት ፍሳሽ  ማጣሪያ እንዲሰሩ  ማድረግ  እንደአቅጣጫ ተይዞ እየተሰራ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

ኢቢሲ

Copyright@2018 Addis Ababa City Resilience Project Office | All Rights Reserved