Blog

የአዋሽ ወንዝ የጎርፍ አደጋ ስጋት ቀንሷል – የተፋሰሱ የጎርፍ መከላከል ግብረ ኃይል

በአዋሽ ወንዝ ሙላት እንደሚደርስ የተገመተው የጎርፍ አደጋ ስጋት መቀነሱን የአዋሽ ተፋሰስ የጎርፍ መከላከል ግብረ ኃይል አስታወቀ።ከሳምንታት በፊት በፌዴራል ደረጃ የተዋቀረው የአዋሽ ተፋሰስ የጎርፍ መከላከል ግብረ ኃይል በአፋር ክልል በሚገኙ የታችኛውና መካከለኛው አዋሽ ተፋሰስ የስጋት ስፍራዎችን ተዘዋውሮ ጎብኝቷል።ግብረ ኃይሉ የጉብኝቱን ማጠቃለያ ግምገማ አስመልክቶ ለኢዜአ እንደገለጸው በአዋሽ ተፋሰስ ይደርሳል ተብሎ የተጠበቀው የጎርፍ አደጋ ስጋት መቀነሱን አረጋግጧል።

አዋሽ በአገሪቱ ከሚገኙ 12 ተፋሰሶች በስፋት የለማና በተፈጥሯዊ የተፋሰስ ባህሪም በክረምት ወቅት ከፍተኛ የጎርፍ መጥለቅለቅ የሚከሰትበት ነው።በዘንድሮ ክረምት በነበረው ከፍተኛ የዝናብ መጠን ትንበያና በአዋሽ ተፋሰስ በሚገኙ ግድቦች ሙላት ሳቢያ በተፋሰሱ የጎርፍ አደጋ እንደሚደርስ ስጋት አሳድሮ ነበር።

ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ለመቀነስም በፌዴራል፣ በኦሮሚያና በአፋር ክልሎች የሚገኙ ባለድርሻ የመንግስት መስሪያ ቤቶችን ያካተተ የጎርፍ መከላከል ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደስራ ተገብቷል።በብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የሚመራውና ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂን፣ ውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክና መከላከያ ሚኒስቴሮችን፣፣ አዋሽ ተፋሰስ ባለስልጣን፣ የኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን፣ ስኳር ኮርፖሬሽን፣ የአፋርና የኦሮሚያ ክልል የአደጋ ስጋት መከላከል ቢሮዎችና ሌሎች ተቋማትን በአባልነት ያቀፈው ግብረ ኃይሉ ለሁለት ቀናት በአፋር ክልል የተፋሰሱን አካባቢዎች ጎብኝቷል።

ከአዋሽ ተፋሰስ ስፍራዎች መካከልም በታችኛው አዋሽ ዱብቲ ወረዳና የተንዳሆ ግድብን፣ በመካከለኛው አዋሽ ደግሞ የገዋኔ፣ አሚባራና አዋሽ ፈንታሌ ወረዳዎች በሚገኙ የአዋሽ ወንዝ የስጋት ቦታዎች እንዲሁም የከሰም ግድብን ተመልክቷል።የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክትል ኮሚሽነር ዳመነ ዳሮታ እንዳሉት በጉብኝቱ በአዋሽ ተፋሰስ ባለስልጣን የተከናወኑ አበረታች የጎርፍ መከላከል ስራዎችና በአንዳንድ ቦታዎች የአዋሽ ወንዝ መስመሩን ሰብሮ በእርሻ ልማት ላይ ጉዳት ማድረሱ ተስተውሏል።

“ውሃ በአግባቡ ከተመራ መልካም እድል ነው” ያሉት አቶ ዳመነ አዋሽ ወንዝ “በክረምት ሽሽት፣ በበጋ ደግሞ የውሃ እጥረት” የሚስተዋልበት ተፋሰስ እንደሆነ በማንሳት ጉብኝቱ በመናበብ፣ በቅንጅትና በባለቤትነት ከተሰራ አደጋን መቋቋም እንደሚቻል ያመላካተ ነው ብለዋል።

ቀደም ሲል በላይኛው አዋሽ ተፋሰስ የመስክ ምልከታ መደረጉን አንስተው በመካከለኛውና በታችኛው ተፋሰሱ የተከናወኑ የቅደመ መከላከል ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የግብረ ኃይሉ አባላት ኃላፊነት ወስደዋል ነው ያሉት።የአዋሽ ተፋሰስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ግዛውም 80 በመቶው የአዋሽ ተፋሰስ ለጎርፍ አደጋ የተጋለጠ መሆኑን ገልጸው፤ ከጎርፍ አደጋ ስጋት ተጋላጭ ያልሆነው የተፋሰሱ ክፍል ከ18 በመቶ እንደማይበልጥ ተናግረዋል።

በዘንድሮው ክረምት ቀደም ሲል በብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ትንበያ መሰረት ባለስልጣኑ ለጎርፍ አደጋ እጅግ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ከ300 ኪሎ ሜትር በላይ የጎርፍ መከላከያ ዱካዎችን የመስራት፣ ነባሩን የማስተካከልና የመጠገን ስራዎች መስራቱን ገልጸዋል።

ከከሰም በስተቀር የቆቃና ተንዳሆ ግድቦች ከሚፈለገው መጠን በላይ ሞልተው አደጋ እንዳያደርሱ የውሃ መጠን የማስተንፈስ ስራዎች መከናወናቸውን አስታውሰዋል።ለጎርፍ አዳጋ ስጋት የነበረው የከሰም ግድብም አሁን ላይ መጠኑ እየቀነሰ በመሆኑ ይደርሳል የተባለው የአደጋ ስጋት መቀነሱን ነው ያብራሩት።

የአዋሽ ወንዝ ከአራት ዓመታት በፊት ሞልቶ ጉዳት ያደረሰው መስከረም 28 እንደነበር በማውሳት መስከረም የክረምት አካል በመሆኑ አሁንም ጥንቃቄ የሚፈልጉ ስራዎች መከናወን እንዳለባቸው የስራ ኃላፊዎቹ ተናግረዋል።ከክረምት ወራት ሙሉ በሙሉ ተወጥቷል ባይባልም በግብረ ኃይሉ ግምገማ ግን ከዚህ በኋላ በተፋሰሱ የከፋ ጉዳት ይኖራል የሚል ስጋት እንደሌለ ነው የገለጹት።

አቶ ዳመነ ዳሮታ እንደተናገሩት ከዚህ ቦኃላ የከፋ ስጋት እንደማይመጣና ነገር ግን ትኩረት አድርጎ ለመስራት ኃላፊነት በመውሰድ በቆይጣቸው አስቀምጠዋል፡፡አቶ ጌታቸው ግዛው በበኩላቸው በዚህ ክረምት ከነበረው ጠንካራ የክረምት ዝናብ አንጻር ቀደም ብለን ያደረግናቸው በቂ ዝግጅቶች ሊደርስ የሚችለውን አደጋ መቋቋም ማስቻሉንና አሁንም የግብረ ኃይሉ ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው ብለዋል፡፡

ኢዜአ

 

Copyright@2018 Addis Ababa City Resilience Project Office | All Rights Reserved