Blog

የአደጋ ሥጋትን በልማት ዕቅዶች ለማካተት የሚያስችል መመርያ ይፋ ተደረገ

ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የአደጋ ሥጋትን በልማት ዕቅድ ሒደቶችና በኢንቨስትመንት ውሳኔዎች ውስጥ አካቶ ለማስፈጸም የሚያግዝ መመርያ ይፋ አደረገ፡፡ መመርያው በተለያዩ የአስተዳደር እርከኖችና የልማት ደረጃዎች የሚገኙ የፌዴራል፣ የክልል፣ የወረዳ፣ የቀበሌና የከተማ አስተዳደር አካላት የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር፣ የቅድመ ማስጠንቀቂያና የምላሽ ሥርዓቶችን በሁሉም የመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ አካተው እንዲፈጸሙ የወጣ መሆኑ ታውቋል፡፡

የስትራቴጂውን ዓላማ ለማስፈጸምም የአደጋ ሥጋት አመራርን በአግባቡ ለመተግበር የሚያስችል የተመቻቸ ሁኔታ መፍጠር፣ ዘርፈ ብዙ የአቅም ግንባታና ዓለም አቀፍ የማቴሪያልና የገንዘብ ድጋፎችን ማቀናጀት ግድ መሆኑ በመመርያው ሠፍሯል፡፡ የአደጋ ሥጋትን በልማት ዕቅዶች ውስጥ በማካተት የመተግበርን አሠራር መስመር ለማስያዝ የተዘጋጀው ይህ መመርያ ይፋ የተደረገው፣ ረቡዕ መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል በተዘጋጀው መድረክ ነው፡፡

የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራርን፣ በመደበኛ የሥራ እንቅስቃሴያቸው ውስጥ በማካተት መተግበር እንዳለባቸውም ታውቋል፡፡ የአደጋ ሥጋት ፖሊሲና ስትራቴጂ የልማት ፕሮግራሞች በልማት ማዕቀፎች፣ በተለይም በመንግሥት፣ በግልና በማኅበረሰብ አቀፍ ልማት ዕቅዶች ውስጥ ተካተው እንዲፈጽሙ ያደርጋል ተብሏል፡፡

ይህም የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራርን አካቶ መተግበር፣ የሥጋት ዳሰሳ ማድረግና መከላከልን የተመለከተ እንደሆነ፣ አሠራሩም ከላይኛው የመንግሥት እርከን እስከ ታችኛው ድረስ በተለያዩ የልማት እንቅስቃሴዎች መቀየር እንዳለባቸው ያመለክታል፡፡

የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንም የስትራቴጂካዊ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ ማዕቀፍ በማዘጋጀት፣ የተለያዩ የአደጋ ሥጋት ቅነሳ ፕሮግራሞችንና ስትራቴጂዎችን በመቅረፅ ወደ ሥራ መግባቱ ተገልጿል፡፡ ከተጀመሩት ፕሮግራሞች ዋነኛውም የወረዳ አደጋ ሥጋት ተጋላጭነት ፕሮፋይል ጥናት ነው፡፡ ጥናቱ በወረዳዎች የሚታየውን የአደጋ ተጋላጭነት፣ ክስተት፣ አቅም፣ መንስዔዎችን ለተለያዩ የአደጋ ቅነሳ ሥራዎች መነሻ መረጃ ያቀብላል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሁሉም የአገሪቱ ገጠራማ ወረዳዎች የተጋላጭነት ፕሮፋይል ጥናት እየተካሄደ መሆኑን፣ የ455 ወረዳዎች ፕሮፋይል መጠናቀቁ ተጠቁሟል፡፡

ኢትዮጵያ በተለይም በድርቅ ምክንያት ሊከሰት የሚችል የኢኮኖሚ ጉዳት ለመቀነስ የሚያስችል አቅም በመፍጠር ረገድ ከዚህ ቀደም ከነበረው የተሻለ መሥራት ብትችልም፣ እየተከሰቱ ያሉ ሰው ሠራሽ አደጋዎች ድርብ ፈተና እንደሆኑባት ይታወቃል፡፡ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስፋት እየተስተዋለ ያሉ ግጭቶችና የዜጎች መፈናቀሎች በኢኮኖሚው ላይ እያደረሱ ያለው ተፅዕኖ አሳሳቢ መሆኑ ይነገራል፡፡

ባለፉት ወራት ተቀስቅሶ በነበረው የጌዴኦና የምዕራብ ጉጂ ግጭት ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡ በቡራዩ ዙሪያ በሚኖሩ ወገኖች ላይ በተፈጸመ ጥቃት በርካቶች ቤት ንብረታቸውን መልቀቃቸው ይታወሳል፡፡ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተቀሰቀሰው ግጭትም በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል፡፡ በጥቂት ወራት ውስጥ በተከሰተው የአገር ውስጥ መፈናቀል ሚሊዮኖች ለጉዳት ተዳርገዋል፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩም ሕይታቸውን አጥተዋል፡፡

‹‹ለአደጋ ያለን ተጋላጭነት በአየር ንብረት ለውጥም ሆነ በውስጥ ግጭቶች እየጨመረ መጥቷል፤›› ያሉት በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የድንገተኛ ጤና አደጋዎች አማካሪ አቶ አስቻለው በላይነህ ናቸው፡፡

ከባለ ድርሻ አካላት መካከል የሆነው ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በሥሩ ከሚገኙ ተጠሪ ተቋማት ጋር በመተባበር ለሚከሰቱ አደጋዎች አፋጣኝ ምላሽ መስጠት የሚያስችለውን አሠራር እየተከተለ መሆኑ ታውቋል፡፡ ሐኪሞችን ጨምሮ የተለያዩ የሕክምና ባለሙያዎቸን ያካተተ ‹‹የአደጋ አመራር አጋዥ ቡድን›› የተባለ ግብረ ኃይል በየሆስፒታሉ ከማዘጋጀት ጀምሮ፣ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለአጣዳፊና እንደ ስኳርና ደም ግፊት ላሉ በሽታዎች የሚሆኑ 78 ዓይነት መድኃኒቶችን የሚይዝ ‹ኪት› በማዘጋጀት አደጋ በተከሰቱባቸው ቦታዎች እንዲደርሱ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በአገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው ሰው ሠራሽ አደጋ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመቆጣጠር ፋታ የነሳ ይመስላል፡፡ ‹‹ዕርዳታ ሕመም ማስታገሻ እንጂ ዘላቂ መፍትሔ አይሆንም፤›› ያሉት ኮሚሽነሩ አቶ ምትኩ ካሳ፣ እንደ ድርቅ ያሉ የተፈጥሮ አደጋዎችን መቋቋም የሚያስችል ዘለቄታዊነት ያለው መፍትሔ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ በአገሪቱ የሚተዋሉ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች የሚያደርሱትን ተፅዕኖ ለመቀነስም፣ የባለድርሻ አካላት ትብብር ግድ እንደሚል ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡

ሪፖርተር

Copyright@2018 Addis Ababa City Resilience Project Office | All Rights Reserved